(ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ): የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ክቡር አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሃት መካከል ለተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ እየገለጸ መሆኑን አንስተዋል።
አምባሳደር መለስ የተፈረመው የሰላም ስምምነት የተለያዩ አገራት፣ የዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፣ ታላላቅ የአገራት ስብስቦች ሁለቱ ወገኖች ግጭት ለማስቆም የደረሱበትን ስምምነት በአዎንታ እንደሚቀበሉትና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጡ የሚያሳዩ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ወታደራዊ አዛዦች እና የህወሃት ወታደራዊ አዛዦች በስምምነቱ መሰረት ኬንያ ናይሮቢ መገናኘታቸው በጎ ጅምር ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።
አምባሳደር መለስ ወዳጆቻችን እና አጋሮቻችን አካላት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ዳግም ለመገንባት የተፈናቀሉትን እንደገና ለማቋቋም ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረትም እንደግፋለን ማለታቸውንም አብራርተዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም ዳያስፖራው ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በመስበክ እንደ የሰላም አርበኝነቱ የወገኖቹ እንባ እንዲታበስ የተፈናቀሉት እንዲቋቋሙ፣የፈረሰው እንዲጠገን ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በዳያስፖራ ማህበረሰብተባብሮ ለመልሶ መቋቋም እና ለልማት እንዲሰራ እናበረታታለን ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ልዩነቶችን እና ጥላቻን ከመስበክ ታቅበው የሰላም ስምምነቱ ፋይዳ እና ትሩፋት ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል፡፡ ቃል አቀባዩ በተለይ አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል ያሳየችበት መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ጉዳዩ አፍሪካዊ መፍትሄ ያግኝ ብላ የፀና አቋም መያዝዋ ጉልህ ውጤት አምጥቷል፡፡
ቃል አቀባዩ ባለፉት ሳምንታት እና ቀናት የተከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ዙሪያም ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በግብፅ ሻርም አልሼክ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ( የCop27 )ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ እና ከባለብዙ ወገን መድረክ በተጨማሪ ከተለያዩ አገራት መሪዎች የዓለም ተቋማት ኃላፊዎች ጋር መወያዬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ክቡር ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች በተካሄደው በ SIR BANI YAS FORUM ላይ ተገኝተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማቶች ለሦስት ሳምንት የሚዘልቅ ስልጠና መስጠት መጀመሩንም ገልፀዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም በሌላ በኩል የኢትዮ ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ ትናንት በይፋ መጀመሩን ገልፀዋል።
ይፋዊ የኤሌክትሪክ ሽያጭ የሚጀምረው ህዳር 5 2015 ዓ/ም ወይም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ህዳር 15 2022 መሆኑንም አብራርተዋል ።

Disclaimer: The official text of the website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram