በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ቆንስል ጄኔራል ክቡር አምባሳደር አክሊሉ ከበደ Air Arabia ከሻርጃ ወደ አዲስ አበባ የጀመረውን አዲስ የቀጥታ በረራ በማስመልከት በሻርጃ አለምአቀፍ ኤርፖርት በተዘጋጀው ይፋዊ የበረራ ማስጀመር መርሃ-ግብር መርቀው በከፈቱበት ወቅት አየር መንገዱ በሳምንት ሦስት ጊዜ የጀመረውን በረራ ሁለቱ ከተሞች ከማስተሳሰር በዘለለ የመከካለኛው ምስራቅ ከአፍሪካን ጋር በማገናኘት የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት እና በቱሪዝም፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው እንዲሁም አዲሱ በረራ በአገራችን እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ማሳያ መሆኑ በዚህ ረገድ የሻርጃ ኤርፖርት እና የአየር ዓረቢያ ላበረረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸው አቅርበዋል፡፡
በመርሃ-ግበሩ የተገኙት የሻርጃህ ኤርፖርት ባለስልጣን ሊቀመንበር አሊ ሳሊም አል ሚድፋ በበኩላቸው በረራው በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና በኢትዮጵያ መካከል እያደገ የመጣውን የጉዞ እና የካርጎ እንቅስቃሴ ፍላጎት ለሟሟላት አጋዥ መሆኑን፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የቱሪዝም ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችል ትስስር የሚፈጥር መሆኑ ገልጸዋል፡፡
የአየር አረቢያ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አደል አል አሊ በበኩላቸው “በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ የቀጥታ በረራዎችን ከሻርጃ ወደ አዲስ አበባ በመጀመራችን ደስ ብሎናል፤ ይህም ለተጓዦች ለንግድም ሆነ ለመዝናኛ ምቹ የጉዞ አማራጮችን በማቅረብ ደስ ብሎናል። አዲሱ በረራ የአየር ትስስርን በማሳደግ የተሳፋሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል” ብለዋል፡፡