የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አፈጻጸም መመሪያ (የልደት፣ጋብቻ፣ፍቺ እና ሞት) የምስክር ወረቀት
የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች፣መስፈርቶች እና ደጋፊ ማስረጃዎች፣
የልደት ምዝገባ
- የልደት ምዝገባ ለማከናወን መሟላት የሚገባቸው ደጋፊ ማስረጃዎች እና መስፈርቶች፡-
- አስመዝጋቢው ጊዜው ያላለፈበት የነዋሪነት/ብሄራዊ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ወይም የመኖሪያ ፍቃድ ወይም ስደተኝነቱን የሚገልጽ ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡
- በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ልደቱ የተከሰተው በጤና ተቋም ከሆነ አስመዝጋቢው ከጤና ተቋም የተሰጠውን የልደት ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡
- የልደት አስመዝጋቢው ከጤና ተቋም የተሰጠውን የልደት ማሳወቂያ ቅጽ ማቅረብ አለበት፡፡ ሆኖም ምዝገባው ከመጀመሩ በፊት የተከሰተን ልደት ምዝገባን አይጨምርም፡፡
- የህጻኑ አሳዳጊ ወይም ተንከባካቢ ልደቱን ለማስመዝገብ ሕጋዊ የአሳዳሪነት ወይም ተንከባካቢነት ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው፡፡
- ዕድሜው አስራ ስምንት ዓመትና በላይ የሆነ ስደተኛ ወላጆቹን የሚገልፅ ማስረጃ ከስደተኞች መረጃ ዳታ ቤዝ ላይ መረጃው የሌለ እንደሆነ ስደተኛውን በመጠየቅ መመዝገብ አለበት፡፡
- የልደት ምዝገባ አገልግሎት ክፍያ 120 ድርሃም ብቻ ነው።
የጋብቻ ምዝገባ
የጋብቻ ምዝገባ ለማከናወን መሟለት የሚገባቸው ደጋፊ ማስረጃዎች እና መስፈረቶች፡-
- ተጋቢዎች ጋብቻ ለመፈፀም ማሰባቸውን እጅግ ቢዘገይ ጋብቻቸውን ለመፈፀም ከወሰኑበት ቀን ከአንድ ወር በፊት ለኢምባሲው ማስታወቅ አለባቸው፡፡ሆኖም ይህ ድንጋጌ በሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስርዓት የሚፈፀም ጋብቻን አይመለከትም፡፡
- የክብር መዝገብ ሹሙ ጥያቄው በቀረበለት ቀን ከተጋቢዎቹ ጋር በመነጋገር ከወሰነ በኃላ በማግስቱ ጋብቻው የሚፈፀምበትን ቀን በመግለጽ አመቺ በሆነው መንገድ ለ15 ተከታታይ ቀን የሚቆይ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡
- ተጋቢዎች ማንነታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው፡፡
- የተጋቢ ምስክሮች አገልግሎቱ ያላለፈበት የነዋሪነት/ብሄራዊ መታወቂያ ወይም የስደተኝነት መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ወይም ሌላ ማንነትን ሊገልፅ የሚችል ማስረጃ መቅረብ አለበት፡፡
- ተጋቢዎች ከዚህ በፊት አግብተው የተፋቱ ከሆነ የፍቺ ምስክር ወረቀት ካለ መቅረብ አለባቸው፡፡
- ከ6 ወር ወዲህ በተመሳሳይ ጊዜ የተነሱት ሁለት ሁለት 3 በ 4 የሆነ የተጋቢዎች ጉርድ ፎቶግራፍ መቅረብ አለበት፡፡
- በባህላዊ ስርዓት የተፈፀመ ጋብቻ የተጋቢዎች ምስክሮች ወይም በጋብቻ ስርዓቱ ላይ የታደመ ሰው በክብር መዝገብ ሹሙ ፊት በአካል ቀርበው ፊርማቸውን ማኖር አለባቸው፡፡
- የተጋቢዎች የልደት ምስክር ወረቀት ካለ መቅረብ አለበት፡፡
- በሙሽራው በኩል 2 በሙሽሪት በኩል 2 በድምሩ 4 ምስክሮች መቅረብ አለባቸው፡፡ሆኖም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 16 መሰረት የተፈፀመ ከሆነ ምስክሮችን በተመለከተ ያለው ክፍት ቦታ በሰረዝ (-) ይታለፋል፡፡
- ተጋቢው ስደተኛ ከሆነ የስደተኝነት እውቅና ያገኘ መሆን አለበት፡፡በማንኛውም ስርዓት የሚፈፀም ጋብቻ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለበት፡፡
- የጋብቻ ምዝገባ አገልግሎት ክፍያ 120 ድርሃም ብቻ ነው።
የፍቺ ምዝገባ
የፍቺ ምዝገባ ለማከናወን መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎችና ደጋፊ ማስረጃዎች፡-
- ፍቺው ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት የተፈፀመ መሆን አለበት፣
- የፍቺ አስመዝጋቢ ሆነው የሚቀርቡት ተፋቺዎች በጋራ ወይም ከተፋቺዎች አንዱ ወይም የተፋቺዎች ልዩ ውክልና ያለው መሆን አለበት፡፡
- ተፋቺው ስደተኛ ከሆነ የስደተኝነት እውቅና ያገኘ መሆን አለበት፡፡
- ፍቺው በፍርድ ቤት የተከናወነ መሆኑን የሚገልፅ የፍርድ ቤት ውሳኔ ግልባጭ መቅረብ አለበት፡፡
- ተፋቺዎች ፍቺውን ለማስመዝገብ ሲመጡ ጊዜው ያላለፈበት የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ፓስፖርት ወይም ማህበራዊ መታወቂያ ወይም ስደተኝነታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው፡፡
- ቀደም ሲል የጋብቻ ምስክር ወረቀት የተሰጠ ከሆነ መመለስ አለበት፡፡
- የፍቺ ምዝገባ አገልግሎት ክፍያ 120 ድርሃም ብቻ ነው።
የሞት ምዝገባ
የሞት ምዝገባ ለማከናወን የሚያስፈልጉ ደጋፊ ማስረጃዎች፣
- ሞቱን ለማስመዝገብ ከጤና ተቋም የተሰጠ ማስረጃ መቅረብ አለበት፡፡
- የሟች ማንነት የሚገልጽ ማሰረጃ ወይም የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ፓስፖርት ወይም ሊሴ-ፓሴ ወይም ማህበራዊ መታወቂያ መቅረብ አለበት፡፡
- የሞት አስመዝጋቢ ከሀገሩ መንግሥት የሞት ምስክር ወረቀት ይዞ መቅረብ አለበት፡፡
- ሞቱ የሚመዘገበው በግለሰቡ መጥፋት ውሳኔ ምክንያት ከሆነ የፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክለኛ ግልባጭ መቅረብ አለበት፡፡
- የሞት ምዝገባ አገልግሎት ክፍያ 80 ድርሃም ብቻ ነው።