በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንሱል ጄኔራል ክቡር አምባሳደር አክሊሉ ከበደ ጥር 08 ቀን 2017 ዓ.ም በዱባይ Police Officers Club በተዘጋጀው Diplomatic Retreat 2025 ላይ ተሳትፈዋል።
በነበረውም የዲፕሎማቲክ ኹነት ላይ የዱባይ ፖሊስን አሠራር ከማዘመን ጋር በተያያዘ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ዙሪያ ገለጻ የተሰጠ ሲሆን በተለይም ተገልጋዮች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ያለሰው ጣልቃ ገብነት የፖሊስ አገልግሎትን የሚያገኙበት እና ከተረኛ የፖሊስ ኦፊሰሮች ጋር በቪዲዮ ጥሪ በመገናኘት መገልገል የሚችሉባቸው Smart Police stations (SPS) ሥርዓት ጋር በተያያዘ ልምዶችን መጋራት ተችሏል።
በተጨማሪም ጊዜው የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የዱባይ ፖሊስን ለማዘመን እየተከናወኑ በሚገኙ ሥራዎች፣ ከሌሎች ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ጋር በተሰሩ ሥራዎች ዙሪያና ሌሎች ገለጻዎች የተሰጡ ሲሆን ይህ ዓይነት የልምድ ልውውጥ በቀጣይ በዘርፉ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ለሚከናወኑ ሥራዎች ጠቃሚ የሚሆኑ ተቋማዊ የልምድ ልውውጦች በይበልጥ እንዲጠናከሩ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ክቡር ቆንስል ጄኔራሉ በኹነቱ ላይ ከዱባይ ፖሊስ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መገናኘትና መነጋገር ችለዋል።