ከቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤታችን እና ከኢትዮጵያውያን ኮሙኒቲ ማህበር የተወጣጣ 4 አባላት ያሉት ቡድን በራስ አልኬማ ማዕከላዊ ማረሚያ ቤት በመገኘት ጉብኝት አካሂዷል። ዛሬ የተካሄደውን የታራሚዎች ጉብኝት ቡድን የመሩት ክቡር አምባሳደር አክሊሉ ከበደ የዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች ቆንስል ጄኔራል ሲሆኑ፣ በማረሚያ ቤቱ በእናትና ልጅ ነፍስ ግድያ ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈርዶባት በሂደት የሞት ፍርዱ ወደ 15ዓመት እስራትና ከ7 መቶ ሺህ ድርሃም (190ሺህ የአሜሪካን ዶላር) በላይ የደም ካሣ ለሟች ቤተሰብ ካሣ እንድትከፍል የተፈረደባትን ኢትየጵያዊ ታራሚ ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች በማረሚያ ቤቱ በሚገኙ 5 ታራሚዎች ጉዳይ ዙሪያ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
በዚህ መሠረት በተለይም በማረሚያ ቤቱ ላለፉት ለአስራ ሁለት ዓመታት በእስር ላይ የቆየችው ዜጋችን የእስር ፍርዱን ያጠናቀቀች ብትሆንም የደም ካሣውን በተመለከተ የራስ አልኬማ ግዛት ፍርድ ቤት ለሟች ቤተሰቦች የወሰነውን የካሣ ክፍያ እንዲፈጸም ከበጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በጋራ በሚሰራበት መንገድ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ታራሚዋንም በማግኘት የምትገኝበትን አጠቃላይ ሁኔታ በመገምገም የማበረታታት እንዲሁም ከጤና ጋር በተያያዘ ያሉባት ችግሮች መፍትሄ እንዲሠጥበት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ታራሚዋ ወንጀሉን ፈጽመው በተያዙበት ወቅት የበርካታ ሚዲያዎች መነጋገሪያ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በማረሚያ ቤቱ 5 ሴቶችና 2 ወንድ ታራሚዎች ይገኛሉ፡፡