ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ቆንሱል ጄኔራል ክቡር አምባሳደር አክሊሉ ከበደ በተገኙበት በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በራስ አልኬማ ግዛት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በዳያስፖራ ተሳትፎ እና በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል። በዚህ ወቅት ክቡር አምባሳደር አክሊሉ ከበደ በሰጡት ማብራሪያ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እና የአገራችን ዋና ዋና የዲፕሎማሲ የትኩረት አቅጣጫዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን አንሰተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዳያስፖራው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አንድነቱን በማጠናከር በአገራዊ ልማቶች፣ በህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢ፣ ሀገራችንን ያጋጠማትን ልዩ ልዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን በጋራ ለመከላከልና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ እና የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት እና መልሶ ለማቋቋም ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም አምባሳደሩ ባስተላለፉት መልዕክት በራስ አልኬማ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከምንግዜውም በተሻለ ሁኔታ በአጋራዊ የማህበራዊና ኢኮሚያዊ ልማት፣ በገፅታ ግንባታ ሥራዎች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው፣ እርስበርስ መደጋገፍ፣ አንድነታቸውን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ገልፀው ለዚህ ደግሞ ባሉበት አካባቢ በተለያዩ የህብረተሰብና የሙያ ዘርፍ መደራጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት ዳያስፖራው እንዲደራጅ፣ በሚኖርበት አገር መብቱና ክብሩ ተጠብቆ ሰርቶ እራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን እንዲጠቅም ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ በማተኮር እየሰራ መሆኑን ክቡር አምባሳደሩ አስረድተዋል። ቆንስላ ጽ/ቤቱ የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ከሀገሩ መንግስት ጋር ከሚሰራው የዲፕሎማሲ ሥራዎች ባሻገር በሰሜን ኤምሬቶች ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማደራጀት ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል ዜጎች እርስበርሳቸው እንዲረዳዱና እንዲተሳሰቡ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበው፣ ከዚህ አንጻር ቆንስላ ጽ/ቤቱ የሁሉም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጋራ መገልገያቸውና ጠባቂያቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በተያያዘም ክቡር አምባሳደሩ በራስ አልኬማ ግዛት የሚፈጠረው የዳያስፖራ አደረጃጀት ከቆንስላ ጄነራል ጽ/ቤት፣ ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር፣ ከሌሎች የተለያዩ የዳያስፖራ ማህበራትና አደረጃጀቶች ጋር ተቀራርበው እና ተቀናጅተው አብረው መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አደረጃጀቱ በተለይ የሁሉም ጥላ እና አቃፊ ከሆነው ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ ቀልጠፋና ግልፅ የሆነ የሥራ ግንኙነትና ቅንጅት ዙሪያ አቶ አየሁ ዳምጤ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር ም/ል ሊቀመንበር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በውይይቱ ከዳያስፖራ አባላት ለቀረቡ የተለያዩ ሀሳበች እና ጥያቄዎች ክቡር አምባሳደሩ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውበታል። በመጨረሻም በራስ አልኬማ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲደራጁ ለማድረግ አሁን ያለውን ጅምር እንቅስቃሴ በማገዝ እና የዕለቱን የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ስፖንሰር ለሆኑ በጎ አድራጊዎች የምስክር ወረቀት በመስጠት እና በቀጣይ በራስ አል- ኬይማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያስተባብር የሴቶች ተሳትፎ የተረጋገጠበት ሰባት የአመራር አባላት በማሰመረጥ የዕለቱ ስብሰባ በተሳካ መልኩ ተጠናቋል፡፡
ራስ አልኬማ በሰሜን ኤምሬቶች ከሚገኙ ግዛቶች አንዷ ስትሆን፣ በተለያዩ ዘርፎች በንግድ፣ በቤት ሰራተኝነት እና በተለያዩ ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚኖሩባት ግዛት ናት። በስብሰባ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል።
 
 
 
 
 
 

Disclaimer: The official text of the website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram