ህዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ክቡር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሌሎች የአገልግሎቱ የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች ከኢትዮጵያዊያን ኮሙኒቲ ማህበር የአመራር ቦርድ አባላት፣ ከሁሉም የዳያስፖራ ማህበራት አመራሮች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሌሎች የዳያስፖራ አባላት ተወካዮች ጋር በዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና ዲጂታል ንቅናቄ፣ በቅርቡ በሀገራችን በመንግስትና በሕወሐት ታጣቂ ቡድን ጋር ሰለ ተደረሰው የሰላም ስምምነት ዙሪያ ውይይት ተደረገ።
በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ቆንሱል ጀነራል ክቡር አምባሳደር አክሊሉ ከበደ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ የውይይት መድረኩን በይፋ በከፈቱበት ወቅት ባሰተላለፉት መልዕክት በዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና ዲጂታል ንቅናቄ ሥራዎች እና በሀገራችን በቅርቡ የተደረሰበት የሰላም ስምምነትን የተመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየት እና በቀጣይ በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን ሊያረጋገጡ በሚችሉባቸው ጉዳዮች፣ ባለፉት ሁለት አመታት እንደ ሀገር ባሳለፍነው ጦርነት የደረሰውን ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መልሰን ልንጠግን በሚያስችሉን ጉዳዮች ዙሪያ መወያየት እጅግ በጣም አንገብጋቢና ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን መሆኑን ገልፀው ክቡር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሌሎች በውይይት መድረኩ የተገኙትን እንግዶች በነዚህ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከዳያስፖራ አባላት ጋር ለመወያየት በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት በውጭ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በያሉበት የሀገራቸውን ክብር እና ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር ላደረጉት ሁሉን አቀፍ አስተዋፅዖ፣ ምንግዜም ከሀገራቸው እና ከወገኖቻቸው ጎን ለመቆም ላደረጉት እንቅስቃሴዎች አድናቆታቸውን ገልፀው በተለይ በሀገራችን በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉትን ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም እና የወደሙ መሰረተ ልማተችን መልሶ ለመገንባት በቅርቡ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሀርና የወገን አለኝታነታቸውን በተግባር ላረጋገጡት ለዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢትዮጵያዊያን ኮሙኒቲ ማህበር እና ለሌሎች ዳያስፖራ አባላት ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡
በተያያዘም ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት በባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገራችንን ሉዓላዊነቷን የሚፈታተኑ ችግሮች የገጠማት ቢሆንም ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ተቋቁማ ሀገራዊ ህልውናዋን ማስቀጠል የተቻላት በልጆቿ ርብርብ እና ቁርጠኝነት መሆኑን ገልፀው በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በሰላም መፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ በመደረሱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። የተደሰበት የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካን ያኮራ ተግባር በመሆኑ የተፈረመው ስምምነት እንዲተገበር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መረባረብ ያለበት ጉዳይ መሆኑን ገልፀው በተለይ ዳያስፖራው የበኩሉን ገንቢ ሚና ሊወጣ የሚገባ መሆኑን አሳስበዋል።
በዚሁ የውይይት መድረክ በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር ክቡር አቶ ቶሌራ ሹላ እና አቶ ነጂብ አልይ የዳያስፖራ ባንኪንግ ሥራ አስኪያጅ ተገኝተው ባንኩ በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ከቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት፣ ከኢትዮጵያዊያን ኮሙኒቲ ማህበር እና ከዳያስፖው ጋር በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ገለፃ ሰጥተዋል።
ክቡር አቶ ኢድሪስ ቡንሱሮ በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢትዮጵያዊያን ኮሙኒቲ ማህበር ሊቀመንበር በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በሀገራችን የተደረሰበትን የሰላም ስምምነት አድንቀው ለተግባራዊነቱ ማኀበሩ እንደ ከዚህ በፊቱ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡ ሌሎች የዳያስፖራ ማኅበራት አመራሮችና የዳያስፖራ አባላት ተወካዮችም በሰጡት አስተያየት ለሀገር ሉዓላዊነት መረጋገጥ፣ ለሰላም ስምምነት ተፈፃሚነት የበኩላቸውን አስተዋፆኦ እንዲሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
እስከ አሁን ኮሚኒቲ ማኅበሩ በተለያዩ ጊዜያት የሚደረጉትን ማንኛውንም ሀገራዊ ጥሪ ተቀብለው ፈጣን ምላሽ በመሰጠት ላደረጉት አስተዋፅኦ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተዘጋጀላቸውን የዕውቅና ሽልማት ከክቡር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ምላሽና ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram